የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የሱፐርቪዥን ቡድን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንን ጎበኘ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሱፐርቪዥን ቡድን በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ግቢ ውስጥ በመገኘት ጉብኝት አድርጓል፡፡
አመራሮቹ በኮሚሽኑ ግቢ ውስጥ እየተገነባ ያለውን ባለ ስምንት ወለል የህንፃ ግንባታ ሒደት ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት የሱፐርቪዥን ቡድኑ አጠቃላይ ተቋሙን ለስራ ምቹ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን የተመለከተ ሲሆን÷ የተካሄዱት ስራዎች አበረታች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
በጉብኝቱ ኮሚሽኑ ከህንፃ ኪራይ ወጥቶ የራሱን ግቢ ለመጠቀም ባደረገው ጥረት ከ78 ሚሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገልጿል፡፡
በቴክኖጂ አጠቃቀም በኩል ከ80 በመቶ በላይ የተቋሙ ተሽከርካሪዎች ጂፒኤስ እንዲገጠምላቸው በማደረግ ከ2 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆን የነዳጅና የንብረት ብክነትን ማዳን መቻሉ ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም ተቋሙ በራሱ ዌብ ፖርታል መጠቀም እንደጀመረ እና የተቋሙ ሰራተኞች በሀገር አቀፍ ደረጃ የተያዘውን የ5 ሚሊየን ኮደርስ ሰርተፊኬት በበይነ መረብ እየሰለጠኑ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን ተቋሙ ባደረገው ንቅናቄ ከፌዴራል እስከ ክልል፤ ዞን እና ወረዳ ድረስ በርካታ ስራዎች መሰራታቸው የተገለፀ ሲሆን÷ በዚህም አበረታች ውጤት ተገኝቷል ተብሏል፡፡
በተቋሙ የተከናወኑ ውጤታማ ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል እና በተቋሙ አፈፃፀም ወቅት የታዩ ክፍተቶችን በቀጣይ እንዲያርም የሱፐርቪዥን ቡድኑ አቅጣጫ መስጠቱን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡