በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ስደተኞች የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው
አሶሳ፤የካቲት 26/2017(ኢዜአ):-በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመጠለያዎች ለሚገኙ ስደተኞች የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሐመድ አብዱላዚዝ እንዳሉት፥ በኢትዮጵያ የስደተኞች መጠለያ በብዛት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች አንዱ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነው።
በተለይም የሱዳን የፖለቲካ ቀውስ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ክልሉ ስደተኞችን በመቀበል የሰብዓዊ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
ክልሉ ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ተቋማት ጋር በመተባበር በክልሉ ዑራ ወረዳ የትምህርት፣የጤናና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ጊዜያዊ ካምፕ እንዲገነባ ማድረጉን ገልጸዋል።
ክልሉ በራሱ አቅም ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አምስት ወረዳዎች ውስጥ ከ27 ሺህ 800 በላይ ከሱዳን የተፈናቀሉ ስደተኞች እንደሚገኙ ተገልጿል።
በሌላ በኩል 13 ሺህ የሚጠጉ የሱዳን ዜጎች በክልሉ ዑራ ወረዳ ጊዜያዊ ካምፕ ተጠልለው በለጋሽ ድርጅቶች ሰብዓዊ ድጋፍ እያገኙ ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን የኢትዮጵያ ተወካይ አንድሪው መብጎሪ፤ ባለፈው ሳምንት በክልሉ ዑራ ወረዳ የሚገኙ ስደተኞችን በጎበኙበት ወቅት በኢትዮጵያ የሱዳን ተፈናቃዮች አያያዝ በጥሩ ሁኔታ ላይ ያለና ለሌሎችም እንደተሞክሮ የሚወሰድ መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል።